የዲዛይን እርክክብ ተደረገ

በወልድያ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አገልግሎት ጽ/ቤት አስተባባሪነት በቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የተዘጋጀ የመንገድና ድልድይ ዲዛይን ስራ ተጠናቆ እርክክብ ተካሂዷል።

በርክክቡ ላይ የተገኙት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር አበበ ግርማ ተቋሙን መልሶ ለማቋቋም ጥረት እያደረግን ብንገኝም እንኳ ያለውን ዕውቀትና ሙያን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ተጠቅሞ የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ እንደመስራት የሚያስደስት ነገር የለም ብለዋል።በቀጣይም ይህንን ተግባር አጠናክረን በመቀጠል በትኩረትና በስፋት ተደራሽ በሆነ መልኩ ይሰራል ያሉት ፕሬዝዳንቱ ወረቀት ላይ ያለውን የዲዛይን ስራም ወደመሬት ወርዶ ማህበረሰቡ ተጠቃሚ ሲሆን ማየት ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል።ዩኒቨርሲቲው ከተሰጡት የመማር ማስተማርና የምርምር ስራዎች በተጨማሪ የማህበረሰብ አገልግሎት ስራ አንዱ ነው ያሉት የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሰለሞን አበጋዝ የማህበረሰብ አገልግሎት ስራ በብዙ ዘርፎች ሊሰሩ የሚችሉ ቢሆንም በተቋሙ ውስጥ የተሻለ የዕውቀት ስብጥር የሚገኝበት በመሆኑ በእንደነዚህ አይነትና መሰል ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት በማድረግ አብዛኛው የአካባቢውን ማህበረሰብ አሳታፊና ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎች ላይ በስፋት እንሰራለን ብለዋል።

በወልድያ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አስራት ተማረ እንደተናገሩት በግዳን ወረዳ ከአባሆይ ጋራ እስከ ወትወት 29 ኪሎ ሜትር መንገድ በውስጡ የሚገኙ የወይን ውሃ ወንዝ ባለ16 ሜትርና የጥራሬ ወንዝ ባለ25 ሜትር ድልድዮች ጨምሮ እንዲሁም ከይባር እስከ አስቂት 13.5 ኬሎ ሜትር የሚረዝም መንገድ በሌላ በኩል በራያ ቆቦ ወረዳ ከተሮ በር እስከ እራማ 10 ኪሎ ሜትር የሚደርስ የመንገድ ዲዛይኖች ከኢንስቲትዩቱ የተለያዩ የት/ት ክፍሎችና ሌሎች ከሚመለከታቸው የት/ት ክፍሎች በተውጣጡ መምህራን ተሰርቶ ከየወረዳወቹ መንገድ ትራንስፖርት ጽ/ቤቶች ጋር እርክክብ መደረግ መቻሉን ገልጸዋል።በስራው ላይ ለተሳተፎ መምህራንና ሌሎች ተባባሪ አካላት ምስጋናቸውን ያቀረቡት ዳይሬክተሩ በቀጣይም ሙያና ሙያ ነክ ስራዎች ላይ በማተኮር ድጋፍ እንደሚደረግ ተናግረዋል።በስራው ላይ ከተሳተፉት መምህራን መካከል በሲቪል ምህንድስና ት/ት ክፍል ውስጥ መምህር የሆኑት መምህር ምላሹ ሲሳይ በርክክቡ ወቅት አጠቃላይ ስለነበረው የስራ ሁኔታ ገለጻ ሲያደርጉ ለሁለቱም ወረዳዎች የተሰሩ የዲዛይን ስራዎች ከ6 ዓመታት በፊት በ2008ዓ.ም በነበረው የዋጋ ስሌት ሲተመኑ 1,993,000 (አንድ ሚሊዮን ዘጠኝ መቶ ዘጠና ሶስት ሽህ ብር) ወጭ እንደሚያስወጡ ተናግረዋል።

በመጨረሻም የተሰራውን የዲዛይን ስራ የተረከቡትና አስተያየታቸውን የሰጡት የግዳን ወረዳ መንገድ ትራንስፖርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ንጉሴ አበባውና በራያ ቆቦ ወረዳ መንገድ ትራንስፖርት ጽ/ቤት ውስጥ የፕሮጀክት ኩንትራት አስተዳደር መሃንዲስ የሆኑት አቶ ዝናቡ አራጌ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው የሰራው ስራ ለመንገዱ መሰራት ከፍተኛውን ድርሻ የሚወስደውን የዲዛይን ስራ መስራት በመቻሉ ያላቸውን ልባዊ ምስጋና በማቅረብ መጠነ ሰፊ የአካባቢውን ማህበረሰብ ችግር ሊፈታ የሚችል ስራ ነው ብለዋል።የመንገዱ መሰራት እናቶች በወሊድ ምክንያት መንገድ ላይ ከመሞት፣ ታዳጊ ህጻናት ትምህርታቸውን ከማቋረጥ እንዲሁም የአካባቢው ማህበረሰብ ያለውን ሃብትና ንብረት ምቹ የገበያ ትስስር በመፍጠር ገቢን ከማሳደግ አንጻር ከፍተኛ የሆነ አስተዋጽኦ አለው ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ የማህበረሰቡ የረጅም ጊዜ ጥያቄ በመሆኑ የተሰራውን የዲዛይን ስራ መሰረት በማድረግና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት በመስራት በአጭር ጊዜ መንገዱን ሰርቶ በማጠናቀቅ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እንሰራለንም ብለዋል።