የወልድያ ዩኒቨርሲቲ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የተሰሩ ተግባራትን አስተዋወቀ

ወልድያ ዩኒቨርሲቲ የኮሮና ቫይረስ/covid-19/ወረርሽኝ ለመከላከል ያከናወናቸውን ተግባራት በጅማ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ባለው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለኮሮና ወረርሽኝ ምላሽ ተግባራት አፈጻጸም ግምገማ መድረክ ላይ ለእይታ አቅርቧል።

በጅማ እየተካሄደ ባለው መድረክ የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ የተለያዩ የሃገሪቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራሮች በተሳተፉበት የከፍተኛ ትምህርት ማስቀጠል ቅድመ ዝግጅትና የተቋማቱን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምላሽ ተግባራት አፈጻጸም ለመገምገም የተጠራውን ሲምፖዚየም ምክንያት በማድረግ በተከፈተው አውደ-ርዕይ የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ለኮሮና ወረርሽኝ ምላሽ ለመስጠት ካከናወናቸው ተግባራት መካከል ዋና ዋናዎቹን ለእይታ አቅርቧል።

ዩኒቨርሲቲው ቫይረሱ ወደሃገራችን ከገባበት ዕለት ጀምሮ በዩኒቨርሲቲውም ሆነ በአካባቢው እንዳይሰራጭና እንዳይስፋፋ በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል።

ካከናወናቸው ተግባራት መካከልም ለአብነት የፀረ ኮረና ግብረ-ሃይል አብይና ቴክኒካል ኮሜቴዎችን በማቋቋም ፓወር ፖይንት በማዘጋጀት በዩኒቨርሲቲው የግንዛቤ ፈጠራ ስራ መስራት፣የውሃ ጎማዎችንና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን በየቦታው የማስቀመጥ፣ተማሪዎችን ወደየ አካባቢያቸው የመሸኘት፣በመኪና በመንቀሳቀስ በሞንታርቦ፣በራሪ ወረቀት በመበተን ፣በዩኒቨርሲቲው ድህረ-ገጽና ራዲዮን በመጠቀም የዋግኸምራ ብሄረሰብ አስ/ርን ጨምሮ በሰሜን ወሎ ዞንና በደቡብ ወሎ አንዳንድ ወረዳዎች በተለያዩ ቦታዎች ግንዛቤ መፍጠር ተችሏል።

ዩኒቨርሲቲው አስፈላጊውን ቁሳቁሶች በማሟላት የለይቶ ማቆያ ማዘጋጀት፣ለሁለቱ ለዋግና ሰሜን ወሎ ዞኖች የተለያዩ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችንና ለለይቶ ማቆያ አገልግሎት የሚውሉ አልጋዎችን ድጋፍ ማድረግ እንድሁም 8 የሚሆኑ የሙቀት መለኪያ ቴርሞ ሜትሮችን በመግዛትና በሁለት ዙር ከ2000 ሊትር/ከ8000 ሚሊ ሊትር/በላይ ሳኒታይዘር በማምረት ይበልጥ ለቫይረሱ ተጋላጭ ለሆኑ አካባቢዎች ማሰራጨት ተችሏል።

በቫይረሱ ምክኒያት የምግብ ዕጥረት የገጠማቸው የማህበረሰብ ክፍሎች በሁለቱ ዞኖች ውስጥ 3500 ለሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ከ1600 ኩንታል በላይ የምግብ እህል ድጋፍ ተደርጓል።

በተጨማሪም የምርመራ ማዕከል በማቋቋም ወደስራ በመግባት እስከአሁን 20000 የሚሆኑ ናሙናዎችን በመመርመር የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል የሚያስችል ስራ እያከናወነ ነው፡፡

በመማር ማስተማሩ ዘርፍ የገጽ ለገጽ ትምህርት ቢቋረጥም የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ስራ ላይ በማዋል ተማሪዎች በየአሉበት ሆነው ትምህርታቸውን በኦንላይን እንዲከታተሉ ማድርግና ሌሎች የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል የሚያስችሉ የተለያዩ የምርምር ስራዎችንም ሲሰራ ቆይቷል እየሰራም ይገኛል።