የወልድያ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ ፕሮግራሞች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች አስመረቀ

ዩኒቨርሲቲው 235 የጤና ሳይንስ ተማሪዎችን ጨምሮ በተለያዩ ፕሮግራሞች በመደበኛ፣ በኤክስቴንሽንና በክረምት መረሃ-ግብር ሲያስተምራቸው የቆዩ 593 የመጀመሪያና የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን በዛሬው ዕለት መጋቢት 16/2015ዓ.ም በግቢው የመመረቂያ አዳራሽ አስመርቋል።የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር አበበ ግርማ፣ የወልድያ ሪጂዮ ፖሊታን ከተማ አስተዳደር ም/ከንቲባና የዕለቱ የክብር እንግዳ የሆኑት ዶ/ር ዳዊት መለሰን ጨምሮ የሴኔት አባላት እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችም በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ተገኝተዋል።


የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አበበ ግርማ በመክፈቻ ንግግራቸው ለተመራቂ ተማሪዎችና አስመራቂ ቤተሰቦች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት በማስተላለፍ በ2013ዓ.ም መጨረሻ ላይ በአካባቢው በነበረው ጦርነት በተቋሙ ላይ ከፍተኛ የሆነ ወድመት በመድረሱ እሱን መልሶ ለማቋቋምና ተማሪዎችን ለማስገባት የነበረውን ፈተና አውስተዋል።ተመራቂ ተማሪዎችም በብዙ ውጣ ወረድ መካከል አልፋችሁ ለዚህ ፍሬ በቅታችኋል ያሉት ፕሬዝዳንቱ በቀጣይም ሊገጥሟችሁ የሚችሉ ፈተናዎችን ሁሉ በጽናትና በብርታት በመወጣት ያለአንዳች ልዩነትና አድሎአዊነት በተማራችሁበት የሙያ ዘርፍ ህብረተሰባችሁን ማገልገል ይጠበቅባችኋል ሲሉ አሳስበዋል።አክለውም የዛሬውን የምረቃ በዓል ልዩ የሚያደርገው የዩኒቨርሲቲው ሶስተኛ ካምፓስ የሆነው የቅዱስ ላሊበላ የቅርስና ቱሪዝም ጥናት ተቋም በሁለተኛ ዲግሪ ያስተማራቸውን ተማሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ማስመረቅ መቻሉ ነው ብለዋል።ቁልፍ ንግግር ያደረጉት የወልድያ ሪጂዮ ፖሊታን ከተማ አስተዳደር ም/ከንቲባና የዕለቱ የክብር እንግዳ የሆኑት ዶ/ር ዳዊት መለሰ በበኩላቸው ተመራቂ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታችሁ ካገኛችሁት የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲገሪ በተጨማሪ የአካባቢውን ወግና ባህል ያያችሁበትም ነው ብለዋል።

የዛሬው ምርቃት ከመጀመርያው ምዕራፍ ወደሁለተኛው ምዕራፍ የተሸጋገራችሁበት ዕለት ነው ያሉት ዶ/ር ዳዊት በቀጣይ ሳይማር ያስተማራችሁን ህብረተሰብ በጽኑ አቋምና ልቦና ያለምንም ልዩነት በታማኝነትና ሃቀኝነት ማገልገል ይጠበቅባችኋል ብለዋል።ስራ ፈላጊነትን ከማማተር ይልቁንም ስራ ፈጣሪ በመሆን ከተቀጣሪነት ወደቀጣሪነት መሸጋገር ይኖርባችኋል ያሉት ዶ/ር ዳዊት ሃገራችን ኢትዮጵያ አሁን ላይ የገጠማትን ችግር በጋራ ልንወጣውና ልናልፈው ይገባናልም ሲሉ ተናግረዋል።ከአጠቃላይ ተመራቂ ተማሪዎች መካከል ከጤና ሳይንስ ኮሌጅ ነርሲንግ ትምህርት ክፍል 4.00 ያመጣው ተማሪ ሲሳይ ተገኘና ከሚድዋይፈሪ ትምህርት ክፍል 3.95 ያመጣችው ተማሪ ወይንሸት ጥላሁን ከብዙ ፈተናዎች በኋላ ለዚህ መብቃት በመቻላቸው እንዳስደሰታቸው ተናግርው በቀጣይም በተማርንበት ሙያና በገባነው ቃለ-ምሃላ መሰረት ያለምንም ልዩነት በፍጹም ታማኝነት ሁሉንም ተገልጋይ ህብረተሰብ ለማገልገል ቆርጠን ተነስተናል ብለዋል።በመጨረሻም ተማሪዎቻቸውን ለማብቃት ጥረት ሲያደርጉ ለቆዩ መምህራንና የመጡበትን አላማ ለማሳካት ሲታትሩ ለቆዩ ተመራቂ ተማሪዎች በተማሪዎች ህብረት አማካኝነት የሽልማትና የዕውቅና ሰርተፍኬት ተበርክቶላቸዋል።በአሁኑ ወቅት ዩኒቨርሲቲው ከሚሰጠው የማህበረሰብ አገልግሎትና የምርምር ስራ በተጨማሪ በመደበኛ፣ በኤክስቴንሽንና በክረምት መርሃ-ግብር ከ18000 በላይ ተማሪዎችን እያስተማረ ይገኛል።