የትግራይ ወራሪ ሃይል በሀገራች ላይ ጦርነት ከፍቶ ታሪክ ይቅር የማይለው ግፍ ፈፅሟል።በተለይም በአማራና በአፋር ክልሎች በተለያዩ ዞኖች ባደረገው ወረራ በወገኖቻችን ላይ ኢ-ሰብዓዊ የሆኑ ድርጊቶችን ፈፅሟል። ከዛ ባሻገር የህዝብ መገልገያ የሆኑ የጤናና የትምህርት ተቋማትን ጨምሮ ሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸውን ተቋማትና መሠረተ ልማቶች በመዝረፍና በማውደም እኩይ የሆነ ተግባሩን በተጨባጭ አሳይቷል። ጥቃት ከተፈፀመባቸው በርካታ መንግስታዊ ተቋማት መካከል ወልድያ ዩኒቨርሲቲ አንዱ ነው።
ዩኒቨርሲቲው በመንግስት ባጀት፣በተለያዩ ጊዚያት የተሳተፋ ስራ አመራር ቦርድ አባላትና የማኔጅመንት አካላት ሰፊ ጥረት፣በአካባቢው ማህበረሰብ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ፣በመምህራ፣በአስተዳደር ሰራተኞቻችንና ተማሪዎቻችን የጋራ ጥረት ተገንብቶ በተለያዩ መርሃ ግብሮች ከ19000 በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ በተለያዩ ፕሮግራሞች በማሰልጠን ላይ የነበረ ተቋም ነው። ከምርምር፣ከማህበረሰብ አገልግሎትና ከመማር ማስተማሩ ባሻገር 3000 ለሚሆኑ ዜጎችም በቋሚና በጊዜያዊነት የስራ እድል በመፍጠር አበርክቶው የጎላ ነው። ተቋሙ ለአካባቢው ማህበረሰብ ብቸኛ ፋብሪካው ነው ብሎ መናገርም ይቻላል።
በሰሜን ወሎዞን መዲና በሆነችው በወልድያ ከተማ የተገነባው ወልድያ ዩኒቨርሲቲ ከተመሠረተ በያዝነው አመት ህዳር ወር ላይ አስረኛ አመቱን ይዟል። ይህንን ታሳቢ በማድረግም የምስረታ በዓሉን በተለያዩ ዝግጅቶች ለማክበር አስፈላጊውን የቅድመ ዝግጅት ስራ ለማከናው መንቀሳቀስ ጀምሮ ነበር።
ተቋማችን ባለፉት አስርት አመታት በነበረው አፈፃፀም የውስጥ ለውስጥ መንገዶቹና አጠቃላይ መሠረተ ልማት ስራዎቹ፣በመምህራን መኖሪያ ቤት ግንባታዎቹ፣በእንግዳ ማረፊያ ህንፃዎቹ፣በመማሪያ ክፍሎቹ፣በአይሲቲ ማዕከል ግንባታው፣ለተማሪዎች አገልግሎት የሚውል የምግብ ማብሰያውና የምግብ ግብዓቶች ማቆያና ማከማቻ ዘመናዊ ህንፃ ግንባታ ጨምሮ በቴክኖሎጂ፣በተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ፣በጤናና በሌሎች የትምህርት ፕሮግራሞች ዘርፍ እጅግ ከፍተኛ በሆነ የውጭ ምንዛሬ ወጭ ለመማር ማስተማሪያነት የተደራጁት ቤተሙከራዎቹ ከራስ አልፈው ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችም የሚገለገሉበትና በአራያነት የሚጠቀስ ተቋም ሆኖ ቆይቷል።በ2013 ዓ.ም በወቅቱ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አማካኝነት በተዘጋጀው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውድድር ሶስተኛው ትውልድ እየተባሉ ከሚጠሩ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል በነበረው የላቀ አፈፃፀም አንደኛ በመውጣት በአስር አመት ጉዞው የደረሰበት ደረጃ እጅግ ተስፋ ሰጭና የሚበረታታ ተቋም እንደሆነም አመላካች ነበር።
ይሁን እንጅ በደረሰው ወረራ በዩኒቨርሲቲያችን ላይ በቃላት ሊገለፅ በማይችል ሁኔታ ከፍተኛ የሆነ ጉዳት ደርሷል።በመርሳና በወልድያ ካምፓስ የተደራጁ ከ120 በላይ ቤተሙከራዎችና ወርክሾፖች፣የተማሪ መገልገያ ዶርሚተሪዎች፣የምግብ ማዘጋጃ ግብዓቶችና መመገቢያዎች፣የህክምና መስጫ ክሊኒክ፣ ቤተ-መፅሃፍት፣የአካዳሚክና የአስተዳደር ቢሮዎች መገልገያ ቁሳቁሶችን በመዝረፍና አገልግሎት እንዳይሰጡ በማበላሸት እንዲሁም ተቋሙ መላው ሀገር ወዳድን አስተባብሮ በአጭር ጊዜውስጥ ስራ እንዳይጀምር በማሰብ በህንፃዎች ላይ የመብራትና የኢንተርኔት ገመዶቸንና ብሬከሮችን ሳይቀር ህንፃ እያፈረሱ ከፍተኛ የሆነ ዝርፊያና ውድመት በማድረስ እኩይ የሆነ ሀሳባቸውን በተግባር ፈፅመዋል።በአጠቃላይ በዩኒቨርሲቲው በደረሰው ጉዳት ከ6 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሆነ በተደረገው ጊዚያዊ ጥናት ታውቋል ።ይህንንን አስከፊ ስራቸውን በመረጃ ተሰንዶ ለታሪክ እንዲቀመጥም ሆነ አለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲያቀው የተለያዩ ኮሚቴዎች ተቋቁመው ከሚዲያዎች ጋርም በጋራ እየተሰራ ይገኛል። እያንዳንዱን የደረሰውን ጉዳትም ሆነ በመልሶ ግንባታው እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ በቀጣይ በዝርዝር እናሳውቃችሗለን።
ይህንን ተቋም በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ መደበኛ ስራው መልሶ አገልግሎት መስጠት እንዲችል ለማድረግ እጅግ ከፍተኛ የሆነ በጀት፣ሙያና ጊዜን የሚጠይቅ ቢሆንም በመንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማትና ግለሰቦች፣በሀገር ወዳድ በሆኑ የዲያስፖራ አባላት፣የኢትዮጵያ ወዳጅ በሆኑ ሀገራት ተሳትፎም ሆነ በመላው ኢትዮጵያውያን ድጋፍና ትብብር እጅግ ባልተራዘመ ሁኔታ የመጀመሪያ አመት ተማሪዎችንና ተመራቂ ተማሪዎችን በቀጣዩ ወር መጨረሻ አካባቢ ሥራውን ለመጀመር የሚያስችል ሁኔታን ለመፍጠር ጥረት እየተደረገ ይገኛል።
የመልሶ ግንባታ ጥረታችን ማገዝ ለምትፈልጉ አጋር አካላትና፤ በአገር ውስጥና ወጭ ያላቸህ በሚከተሉት የኢሜል አድረሻ ማግኘት ትችላላቹህ፡፡
President office: info@wldu.edu.et
ICT Directorate: ictd@wldu.edu.et
በተጨማሪ ወራሪው ሀይል ያሳደረውን ጉዳት እሚያሳይ ቪዲዮ በዩቲዩብ ቻናላችን እምንጭነው ይሆናል።