ዩኒቨርሲቲው በ40 የትምህርት መስኮች በመደበኛ፣በኤክስቴንሽንና በክረምት መርሃ ግብር ያሰለጠናቸውን 2785 ተማሪዎችን የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስተር የደህንነትና ፀጥታ አማካሪ ሚኒስትር ክቡር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል ማህበራዊ ዘርፍ ክላስተር አስተባባሪና የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሀላፊ ክብርት ዶ/ር ሙሉነሽ አበበ፣በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የማህበረሰብ አገልግሎት ጀኔራል ዳይሬክተር ዶ/ር ሰለሞን ቢኖር፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር አማካሪና የቀድሞው የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ያለው እንዳወቀ፣የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ስራ አመራር ቦርድ ም/ሰብሳቢ አቶ ወልደ ትንሳኤ መኮንን፣ከፌደራል፣ከክልል፣ከዩኒቨርሲቲወች፣ከዞንና ከከተማ አስተዳደሩ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡እንዲሁም የአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎች፣የሀይማኖት አባቶችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በሼህ ሙሃመድ ሁሴን አሊ አላሙዲን ስታዲየም በደማቅ ሁኔታ ተካሂዷል።
የዕለቱ ልዩ የክብር እንግዳ በመሆን የተገኙት የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስተር የደህንነትና ፀጥታ አማካሪ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እንደተናገሩት ትምህርት የሀገርን ችግር ለማስወገድ ከፍተኛ የሆነ ሚና እንዳለው በመናገር መንግስት ትምህርት ለሀገር ዕድገት ማሳለጫ ወሳኝ መሳርያ መሆኑን በመረዳት በዚህም ዘርፍ ከፍተኛ የሆነ ኢንቨስትመንት በማድረግ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን እያስፋፋ ይገኛል ብለዋል።
አክለውም ተመራቂ ተማሪዎችም ያገኛችሁትን ዕውቀትና ክህሎት በቅንነትና በታማኝነት ሀገራችሁንና ወገናችሁን እንድታገለግሉ ሲሉ አሳስበዋል።የክልሉን መንግስት በመወከል የተገኙት የአብክመ በም/ርዕሰ መስተደድር ማዕረግ የማህበራዊ ዘርፍ አስተባብሪና የክልሉ ሰራተኛና ማህበራዊ ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሙሉነሽ አበበ በበኩላቸው ትምህርት የህይወትን ሚስጥር መክፈቻ ዋነኛ ቁልፍና ለሀገር ዕድገት ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
ሀገራችን ኢትዮጲያ ባለብዙ ጸጋ ባለቤት መሆኗን እኛ ቀርቶ መላው አለምም ምስክሮች ናቸው ያሉት ዶ/ር ሙሉነሽ ይህንንም በመማር፣በመመራመር፣በመጠየቅና ጉዳዮችን በአንክሮ በመመልከት ሀገራችን ለገጠማት ውስብስብ ችግሮች መፍትሄ በማፈላለግ በቀጣይ የብልጽግና ጉዞዋን በማፋጠን የነበረንን ገናናነት በመመለስ ለሌሎች ሀገሮች ተምሳሌት መሆን ያስፈልጋል ብለዋል።
የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አበበ ግርማ በበኩላቸው ከብዙ ውጣ ውረድ በሗላ በተለይም ባለፈው አመት የተከሰተውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ተቋቁማችሁ ለዚህ የበቃችሁ ተመራቂ ተማሪዎችና የተመራቂ ተማሪ ቤተሰቦችን እንኳን ደስ አላችሁ በማለት በስነ ምግባር የታነጸ፣በዕውቀት የዳበረ፣በተግባር የተደገፈና በሀሳብ ልዕልና የምናምን ትውልድ መሆን ይጠበቅብናል ብለዋል። አክለወም ዩኒቨርሲቲው ከተመሰረተ ጀምሮ ከመማር ማስተማሩ ጎን ለጎን በርካታ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎችን ሲያከናውን የቆየና እያከናወነም ያለ መሆኑን ተናግረዋል።
በዩኒቨርሲቲው ከአጠቃላይ ተመራቂ ተማሪዎች መካከል 3.99 ውጤት በማምጣት የዋንጫ ተሸላሚ የሆነችው ተማሪ ህይወት ፈንታው ከብዙ ችግሮች በኋላ ለዚህ መብቃቷ እንዳስደሰታት በመናገር ለዚህ እንድትበቃ ላደረጓት ሁሉ ምስጋናዋን አቅርባለች። ለአላማችን ከቆምን የማይሆንና የማይሳካ ነገር የለምና ሁላችንም አላማችንን ለማሳካት ትኩረት ማድረግና መጣር ያስፈልጋል ያለቸው ተማሪ ህይወት በቀጣይም በተማርኩበት የሙያ መስክ ያስተማረኝን ህብረተሰብና ሀገሬን ለማገልገል ቁርጠኛ ሁኜ እሰራለሁ ብላለች።