በወልድያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን መልሶ ለመቀበል የሚያስችል የዝግጅት ምዕራፍ ግምገማ ተካሄደ፡፡

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን በመከላከል የበሽታውን ስርጭት ለመግታትና ተማሪዎችን መልሶ ለመቀበል የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ለመገምገም በዩኒቨርሲቲው ግቢ የተገኙት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የድጋፍና ክትትል ቡድን ከዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንት አባላት፣ ከአካዳሚክና አስተዳደር ዘርፍ የስራ ክፍል ሃላፊዎች ፣ ከተማሪዎች መማክርትና ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት አካሂደዋል፡፡ ባደረጉት የመስክ ምልከታም ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችን ለመቀበል ያለበትን ቁመና ይዘውት በመጡት ቼክ ሊስት መሰረት ገምግመዋል።በጉብኝቱ የመምህራን ዝግጅት፣ የቤተ-ሙከራና ቤተ-መፃህፍት፣ መማሪያ ክፍሎችና የተለያዩ ወርክ ሾፖች ምቹ በሆነ መልኩ መደራጀታቸውን፣ የተማሪዎች መኝታ ቤት በአንድ ክፍል ሁለት ተማሪ፣በመማሪያ ክፍል እስከ 30 የሚደርሱ ተማሪዎችን በመመደብ የመማር ማስተማር ስራውን ለማስቀጠል መወሰኑ የሚበረታታ ተግባር እንደሆነ ተገልፀዋል ፡፡ የግቢው መሠረተ ልማትና ጽዳቱን በተመለከተ ሳቢ ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት፣ የምግብ ማብሰያ ኪችኖች እድሳትና ተጨማሪ ግንባታ እንዲሁም በሬጅስትራር በኩል ከሰው ንክኪ ነፃ የሆነ አሰራር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትንም በጥንካሬ አንስተዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ቀደም ብሎ ከነሃሴ 7/2012 ዓ.ም ጀምሮ ከተለያዩ የስራ ክፍሎች የተወጣጡ አባላትን ያካተተ የዝግጅት ምዕራፍ ዕቅድ ስራዎችን የሚያቅድና አፈፃፀሙን የሚገመግም የሱፐርቪዥ ኮሚቴ አቋቁሞ ወደ ስራ መግባት መቻሉ የነበሩ ክፍተቶችን ለይቶ ለመስራት እንዳስቻለና ይህም ለሌሎች ተሞክሮ የሚሆን እንደሆነም በውይይቱ ተነስቷል፡፡ በሌላ በኩል በቀላሉ ሊተገበሩ የሚችሉ ከንክኪ ነፃ የሆነ የእጅ መታጠቢያዎችን በስፋት ማቅረብ፣ የቴክኖሎጅ ፈጠራ ስራዎች ላይ ትኩረት ማድረግ፣የግንዛቤ ፈጠራ ስራዎችን ማጠናከርና ስልጠና መሰጠት እንዲሁም በቀላሉ ሊፈፀሙ የሚችሉ የተጀመሩና ሂደት ላይ ያሉ ተግባራትን አጠናክሮ በመቀጠል ሊፈጸሙ እንደሚገባም በአስተያየታቸው ተጠቁሟል፡፡ዩኒቨርሲቲው ተጨማሪ ከ30 በላይ የሚሆኑ የዋይፋይ አገልግሎት ለመስጠት እያደረገ ያለውን ጥረት የሚበረታታ ቢሆንም በአስቸኳይ ተጠናቆ አገልግሎት እንዲሠጥም ሀሳባቸውን አንስተዋል ፡፡በአጠቃላይ በዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች መቼ ይጠራሉ የሚለው ሀሳብ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የድጋፍና ክትትል ቡድንን ግብረ መልስ መሠረት አድርጎ ይፋ በሚያደረገው ቀን መሠረት ጥሪ እንደሚተላለፍ የሱፐርቪዥን ቡድኑ ተናግረዋል፡፡
መስከረም 26/2013ዓ.ምወልድያ ዩኒቨርሲቲ