በወልድያ ዩኒቨርሲቲ በሁለቱም ካምፓስ ለሚገኙ ሴት መምህራን የአመራርነትና አስተዳደር ስልጠና ተሰጠ፡፡ ከታህሳስ 22-23/2013 ዓ.ም በዩኒቨርሲቲው ዋና ግቢ በተዘጋጀው ስልጠና የዩኒቨርስቲው ሴት መምህራን ተሳታፊ መሆናቸውን የስልጠናው አስተባባሪ የሆኑት የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ዋጋየ ሞላ ተናግረዋል ፡፡
አያይዘውም የስልጠናው ዓላማ በዩኒቨርሲቲያችን ብሎም በሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሴት አመራር ቁጥራቸው በመቀነሱና በተለይ የከፍተኛ አመራር ቦታዎች ሙሉ በሙሉ በወንዶች በመሸፈኑ ሴቶችን በአመራርነት ላይ ያላቸውን ችሎታ አቅም እንዲያዳብሩና ተነሳሽነት እንዲያሳዩ በማድረግ ወደ አመራርነት እንዲመጡ ለማድረግ መሆኑን ወ/ሮ ዋጋየ ሞላ ገልፀዋል፡፡
ስልጠናውን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርትና የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ስራ አመራር ቦርድ አባል የሆኑት ፕ/ር ያለም ፀሀይ መኮነን የሰጡ ሲሆን በረጂም ጊዜ የስራና የህይዎት ልምዳቸው ያካበቱትን ዕውቀትና ክህሎት በዋቢነት በመጥቀስና ለስኬታቸው ምክንያት ናቸው ያሏቸውን የህይወት ተሞክሮዎች አካፍለዋል፡፡
ሰልጣኞችም ከዚህ ስልጠና በኋላ የራሳቸውን ግብ ቀርፀው በመውጣትና ባሉበት የትምህርትና የህይወት ጉዞ ሳይገደቡ ለስኬት መጓዝ እንዳለባቸው ፕሮፌሰሯ አጽኖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡በመጨረሻም ሰልጣኞቹ ከስልጠናው በርካታ ልምዶችና ተሞክሮዎችን እንዳገኙበት፤እርስ በእርስ እዲማማሩና እንዲተዋወቁም ጭምር እንዳደረጋቸው ገልፀው የዚህ አይነት ስልጠናዎች ቀጣይነት ቢሮራቸው እነሱም ለሴት ተማሪዎቻቸው አርዓያ ለመሆን የሚችሉበት ደረጃ ላይ መድረስ እንዲችሉ ትልቅ አቅም እንደሚሆናቸው ገልፀዋል፡፡