• Main Gate

Events Calendar

February 2019
S M T W T F S
27 28 29 30 31 1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 1 2

Latest Events

No events

9ወር ዕቅድ አፈጻጸም ላይ ውይይት ተካሄደ

13/08/08 . በዩኒቨርሲቲው ግቢ DSTV አዳራሽ በተዘጋጀው መድረክ የቀረበውን 9ወር ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት መሰረት በማድረግ ውይይት ተካሄደ፡፡

በውይይቱ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ያለው እንዳወቀን ጨምሮ ሌሎች ሁሉም ምክትል ፕሬዚዳንቶች፣ዲኖች፣ ዳይሬክተሮችና መላው የዩኒቨርሲቲው መምህራንና ሰራተኞች እንዲሁም የተማሪ ተወካዮች ተሳትፈውበታል፡፡ በውይይቱ መጀመሪያ ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ያለው እንዳወቀ ሰሞኑን በሃገራችን የጋንቤላ ክልል ነዋሪ በሆኑት ወገኖቻችን ላይ በተፈፀመው -ሰባዊ የሆነ ድርጊት ህይወታቸው ላለፉ ሰላማዊ ነዋሪዎች 1 ደቂቃ የህሊና ፀሎት በማድረግ እንድናስባቸው አድርገዋል፡፡ በመቀጠልም በማህበረሰቡ ላይ የደረሰውን ጉዳት መሰረት በማድረግ መንግስት አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድም ጠይቀዋል::

 

በጋምቤላ ክልል ህይወታቸው ላለፉ ወገኖቻችን የህሊና ፀሎት ሲደረግ

 

9 ወር የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ ጋር በተያያዘም ዕቅዱ የሁላችንንም የስራ ክፍል መሰረት ያደረገና በጋራ ገምገመን ያፀደቅነው መሆኑን አስታውሰው አፈጻጸሙንም በጋራ መገምገም ራዕያችንን ለማሳካት በምናደርገው ጉዞ ላይ ወሳኝ በመሆኑ መድረኩ ተመቻችቷል ብለዋል ፡፡ አክለውም ይህንኑ መነሻ በማድረግ ሁሉም ተሳታፊዎች አዕምሯችንን ክፍት በማድረግ በሚቀርበው ሪፖርት ላይ የበሰለ አስተያየትና ጥያቄዎችን በማንሳት የተሳካ ውይይት እንድናደርግ ሁላችንም በንቃት ልንሳተፍ እንደሚገባ አሳስበዋል ፡፡


 

የዩኒቨርሲቲው ፕላን ፕሮግራምና በጀት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተፈራ ተስፋዬ የዩኒቨርሲቲውን ግቦች መነሻ በማድርግ ባቀረቡት ሪፖርት ተሳታፊዎች ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን አንስተዋል ፡፡ ከተነሱት መካከል በአካዳሚክ ዘርፍ ከመማሪያ ቁሳቁሶች ጋር በተያያዘ በቂ የሆነ LCD አለመሟላት ፣የተደራጁ ቤተሙከራዎች አለመኖር፣ አንዳንድ መማሪያ ክፍሎች ላይ የተሰባበሩ ወንበሮች መኖርና 3 ድግሪ ተማሪዎች የጥቅማ ጥቅም ጉዳይ ላይ ትኩረት ተደርጎ የተነሱ ሲሆን ከምርምር ጋር በተያያዘም ለተመራማሪዎች የሚመደበው በጀት አናሳ መሆን፣ ወጣትና ጀማሪ ተመራማሪዎችን ከመደገፍና ከማበረታታት ይልቅ ፍጹማዊነትን መጠበቅ የመሳሰሉት ተነስተዋል ፡፡ በግንባታና መሰረተ ልማት በኩልም የተሰሩት የውሃ መፍሰሻ ቦዮች ከፍት መሆናቸው ለአካል ጉዳተኞች ምቹ አለመሆን፣ የደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ላይ ትኩረት ተደርጎ ቢሰራ የሚል አስተያየቶች ተሰጥተዋል፡፡


 

በአጠቃላይ ከበጀት አጠቃቀማችን ጋር ተያይዞ ያለንን በጀት በቀሪዎቹ ወራቶች ላንጠቀምበት እንችላለን በበጀት አጠቃቀምና በሂሰብ አመዘጋገብ ላይ ክፍተት አለ ፣እቅዱና አፈጻጸሙ በንጽጽር የሚቀርብበት ሁኔታ ቢፈጠር የሚሉት ጥያቄና አስተያየቶችም ከተነሱት መካከል ዋና ዋናዎቹ ናቸው ፡፡

በአካዳሚኩ ዘርፍ በተሳታፊዎቹ የተነሱትን ጥያቄና አስተያየቶች መሰረት በማድረግ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሰይድ ሁሴን ምላሽ ሰጥተውባቸዋል ፡፡ ከቤተሙከራ አለመደራጀት ጋር በተያያዘ በተነሳው ጥያቄ ችግሩን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመቅረፍ ከመከላከያ ኢንጅነሪንግ ኮርፓሬሽን ጋር 41 ሚሊዮን ብር ወጭ 30 የቤተ-ሙከራ ክፍሎችን ለማደራጀት ስምምነት ላይ ተደረሶ 12 ሚሊዮን ብር ቅድሚያ ክፍያም ተፈፅሟል ብለዋል ፡፡ 3 ዲግሪ ተማሪዎች ጉዳይም አንዳንድ ጥቅማ ጥቅሞችን ለማስከበር በማኔጅመንቱ የተወሰነ በመሆኑ በጀቱ ካለን በዚህ አመት ከሌለን ደግሞ ከሃምሌ 1 ጀምሮ እንደሚስተካከልላቸው ጠቁመዋል፡፡ ከትምህርት ግብዓት ጋር ተያይዞ የተነሳው LCD ፕሮጀክተር ችግርም በቅርቡ ግዥ ተፈፅሞ እንደሚከፋፈል አስረድተዋል ፡፡

በሌላ በኩል አቶ ገበያው ጥላሁን በምርምር በኩል የተነሱትን ጠያቄዎች በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል ፡፡ ባለፉት አራት አመታት ጀማሪነታችንን ግምት ውስጥ በማስገባት ስንሰራ የቆየን መሆኑን ጠቅሰው በዚህ ሁኔታ መቀጠል ደግሞ መንግስት የሚፈልገውን ችግር ፈች የምርምር ውጤቶችን እንዳንሰራ ያደርገናል ብለዋል ፡፡

አያይዘውም ለምርምር የሚመደበው በጀት በቂ እና ብክነትን የማያስከትል አከፋፋል እንደሆነ ገልጸው ምንም እንኳ በምርምር ስራ ላይ የበጀት ዕጥረት ቢገጥም በመመሪያው መሰረት በቂ መረጃ ከቀረበ መጨመር እንደሚቻል ተናግረዋል ፡፡

ከግንባታና መሰረተልማት አኳያ ደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻን ችግር በዘላቂነት ለማስወገድ የሚያስችል የኦክስደሽን ፖንድ ግንባታ በመካሄድ ላይ በመሆኑ በቅርብ ቀን መፍትሄ እንደሚገኝ የግንባት ፕሮጀክት /ቤት ኃላፊ አቶ ምናየ ገበየሁ ገልጸው የውሃ መፍሰሻ ቦዮች ክፍት መሆን ግን ትምህርት ሚኒስቴር ወጭ ቆጣቢ በሚል እሳቤ ያዘጋጀው ዲዛይን በመሆኑ አሁን ማስተካከል እንደማይቻል ተናግረው በቀጣይ ግን ማሻሻያ እየተደረገ እንደሚስተካከል አስረድተዋል፡፡

በአጠቃላይ በውይይቱ የተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ላይ የሚመለከታቸው ሌሎች የስራ ክፍሎችም ማብራሪያና ምላሽ ሰጥተውባቸዋል ፡፡

በውይይቱ በዩኒቨርሲቲው በለውጥ ስራዎች ላይ እየታየ ያለው መልካም መነቃቃት የሚበረታታ በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም ተጠቁሟል ፡፡

 

 


 

Last Modified Date

 November 21, 2018, 1:28 pm 

Copyright © 2014. Woldia University. All Rights Reserved.